
ፆመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚታሰብበት ወቅት ![]() ይህ ጾመ ፍልሰታ በሌላ አጠራሩ ጾመ ማርያምም በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ወቅት በብዛት የሚወሳው /የሚነገረው/ቃለ እግዚአብሔር በአብዛኛው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የተያያዘ በመሆኑና የእርስዋ የሥጋዋ ፍልሰት መታሰቢያ በመሆኑ ጾመ ማርያም ተባለ፡፡«ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፣ ተሰደደ ከሚለው ግስ የወጣ ነው፡፡ ፈለሰ ማለት ደግሞ የተለያየ ትርጉም ቢሰጠውም ፍልሰታ ለማርያም ብሎ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ወደ ማያልፈው ዓለም ከመቃብር የወጣችበት /የተነሣችበት/ ቀን ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሥጋዊው ዓለም ወደ መንፈሳዊው ዓለም የተሸጋገረችበት ነው፡፡» አበው"ሞትኪሰ ማርያም ይመስል ከብካበ"እንዳሉት የእመቤታችን እረፍት እንባ መራጨት፣ ጠጉር መንጨት፣ ደረት መድቃት እንዳለበት የሰው ሞት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንደ ሠርግ ቤት መላዕክት በውዳሴ፤ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና ወደ ሰማይ ሸኟት፡፡ እንጂ ቅዱስ ያሬድም"ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ" እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለች፡፡ በዚያም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች በማለትም ዘምሯል፡፡ የእመቤታችን ሥጋዋ ከጌቴሴማኔ ወደ ገነት መፍለሱን አስቀድሞ አባቷ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት ሲናገር "ተንስእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ" አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት በማለት ተንብዮዋል፡፡ መዝ. 131፡8 ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንአት መንፈስ ተነሣሥተው «ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን) ኑ ተሰብሰቡና ሥጋዋን በእሳት እናቃጥላት» ብለው ተማክረው መጡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን አጎበር (የአልጋ ሸንኮር) በድፍረት ያዘ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ በእውነት የአምላክ እናት ናት በማለት ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደነበሩ ሆነውለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ በ14 (በሁለተኛው ሱባኤ መጨረሻ) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ ዕረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት በተፈጸመ ጊዜ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ፣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ቀድሞ የልጅሽን አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራው ቅዱስ ቶማስን አጽናናችው፡፡ ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ለምልክት ይሆነው ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወደ አሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ «የእመቤታችን ነገር እነዴት ሆነ?» ብሎ ቢጠይቃቸው፤ «እመቤታችንን እኮ ቀበርናት» ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ዐውቆ ምስጢሩን ደብቆ «አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?» አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው፡፡ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም ብሎ የእመቤታችን መካነ መቃብር ሊያሳዩት ይዘውት ሔዱ፡፡ መቃብሩን ቢከፍቱ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አጡት፤ ደነገጡም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች» ብሎ የሆነውን ሁሉ ተረከላቸው፡፡ ከዚያም ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ እነርሱም ማረጓን አምነው ሰበኗን ለበረከት ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄዱ፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምር ሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡
በዓመቱ
ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እንዴት ይቅርብን
ብለው ነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ፡፡
በሱባኤው መጨረሻ ነሐሴ 16
ቀን
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የለመኑትን ልመና ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣
ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቀ (ረዳት)
ቄስ)፣
ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ (ዋና)
ዲያቆን
አድርጎ ቀድሶ አቁርቦአቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ
እመቤታችንን ሐዋርያት በግልጽ ትንሣኤዋን
ዕርገቷን እያዩዋት ከጌታችን ጋር በክብር
በይባቤና በመዝሙር ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡
ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ «እመቤታችን
ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች
በሰማይም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ
ቀኝ ተቀመጠች»፡፡
የትንሣኤያችን በኲር የሆነው የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነቱ ከሁላችን ጋር ይሁን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን። በረከቷ፤ ፍቅሯ፤ ጣዕሟ በእኛ በልጆቿ ላይ አድሮ ይኑር አሜን፡፡ | የፌስቡክ ገጻችን ተከታይ ይሁኑ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ
English Bible
|
